• 1. ፀሐይ በተጠቀለለች ጊዜ፤

  • 2. ከዋክብትም በረገፉ ጊዜ፤

  • 3. ተራራዎችም በተነዱ ጊዜ፤

  • 4. የዐሥር ወር እርጉዞች ግመሎችም (ያለጠባቂ) በተተዉ ጊዜ፤

  • 5. እንስሳትም ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜ፤

  • 6. ባሕሮችም በተቃጠሉ ጊዜ፤

  • 7. ነፍሶችም (በየአካሎቻቸው) በተቆራኙ ጊዜ፤

  • 8. በሕይወቷ የተቀበረችውም ሴት ልጅ በተጠየቀች ጊዜ፤

  • 9. በምን ወንጀል እንደ ተገደለች፤

  • 10. ጽሑፎችም በተዘረጉ ጊዜ፤

  • 11. ሰማይም በተገሸለጠች ጊዜ፤

  • 12. ገሀነምም በተነደደች ጊዜ፤

  • 13. ገነትም በተቀረበች ጊዜ፤

  • 14. ነፍስ ሁሉ (ከሥራ) ያቀረበችውን ታውቃለች፤

  • 15. ተመላሾችም በኾኑት (ዐዋድያት) እምላለሁ፡፡

  • 16. ኺያጆች ገቢዎች በኾኑት (ከዋክብት)፡፡

  • 17. በሌሊቱም (ጨለማውን) በጠነሰሰ ጊዜ፤

  • 18. በንጋቱም (በብርሃን) በተነፈሰ ጊዜ፤ (እምላለሁ)፡፡

  • 19. እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡

  • 20. የኀይል ባለቤት በዙፋኑ ባለ ቤት ዘንድ ባለሟል የኾነ፡፡

  • 21. በዚያ ስፍራ ትእዛዙ ተሰሚ፤ ታማኝ የኾነ (መልክተኛ ቃል) ነው፡፡

  • 22. ነቢያችሁም በፍጹም ዕብድ አይደለም፡፡

  • 23. በግልጹ አድማስም በእርግጥ አይቶታል፡፡

  • 24. እርሱም በሩቁ ወሬ ላይ ሰሳች (ንፉግ) አይደለም፡፡

  • 25. እርሱም (ቁርኣን) የእርጉም ሰይጣን ቃል አይደለም፡፡

  • 26. ታዲያ ወዴት ትኼዳላችሁ?

  • 27. እርሱ የዓለማት መገሠጫ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡

  • 28. ከናንተ ቀጥተኛ መኾንን ለሻ ሰው (መገሰጫ ነው)፡፡

  • 29. የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo