• 1. መሰለፍን በሚሰለፉት፡፡

  • 2. መገሠጽንም በሚገሥጹት፤

  • 3. ቁርኣንንም በሚያነቡት እምላለሁ፡፡

  • 4. አምላካችሁ በእርግጥ አንድ ነው፡፡

  • 5. የሰማያትና የምድር በመካከላቸው ያለውም ፍጡር ሁሉ ጌታ ነው፡፡ የምሥራቆችም ጌታ ነው፡፡

  • 6. እኛ ቅርቢቱን ሰማይ በከዋክብት ጌጥ አጌጥናት፡፡

  • 7. አመጸኛም ከሆነ ሰይጣን ሁሉ መጠበቅን ጠበቅናት፡፡

  • 8. ወደላይኛው ሰራዊት አያዳምጡም፡፡ ከየወገኑም ሁሉ ችቦ ይጣልባቸዋል፡፡

  • 9. የሚባረሩ ሲሆኑ (ይጣልባቸዋል)፡፡ ለእነሱም ዘውታሪ ቅጣት አላቸው፡፡

  • 10. ንጥቂያን የነጠቀ ወዲያውም አብሪ ኮከብ የተከተለው ሲቀር፤ (እርሱ ይሰማዋል)፡፡

  • 11. ጠይቃቸውም፤ እነርሱ በአፈጣጠር ይበልጥ የበረቱ ናቸውን? ወይስ እኛ (ከእነርሱ በፊት) የፈጠርነው? (ፍጡር) እኛ ከሚጣበቅ ጭቃ ፈጠርናቸው፡፡

  • 12. ይልቁንም (በማስተባበላቸው) ተደነቅህ፤(ከመደነቅህ) ይሳለቃሉም፡፡

  • 13. በተገሠጹም ጊዜ አይመለሱም፡፡

  • 14. ተዓምርን ባዩም ጊዜ ለመሳለቅ ይጠራራሉ፡፡

  • 15. ይላሉም «ይህ ግልጽ ድግምት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

  • 16. «በሞትንና ዐፈርና አጥንቶችም በኾን ጊዜ እኛ የምንቀሰቀስ ነን?

  • 17. «የቀድሞዎቹ አባቶችንም? (ይላሉ)፡፡

  • 18. «አዎን እናንተ ወራዶች ሆናችሁ (ትነሳላችሁ)» በላቸው፡፡

  • 19. እርሷም አንዲት ጩኸት ብቻ ናት፡፡ እነርሱም ወዲያውኑ (ምን እንደሚፈጸምባቸው) ያያሉ፡፡

  • 20. «ዋ ጥፋታችን! ይህ የፍርዱ ቀን ነው» ይላሉም፡፡

  • 21. «ይህ ያ በእርሱ ታስተባብሉ የነበራችሁት መለያው ቀን ነው» (ይባላሉ)፡፡

  • 22. (ለመላእክቶችም) «እነዚያን ነፍሶቻቸውን የበደሉትን ሰዎች ጓደኞቻቸውንም ይግገዟቸው የነበሩትንም (ጣዖታት) ሰብስቡ፡፡

  • 23. «ከአላህ ሌላ (የሚገዙዋቸውን ሰብስቧቸው) ወደ እሳት መንገድም ምሩዋቸው፡፡

  • 24. «አቁሟቸውም፡፡ እነርሱ ተጠያቂዎች ናቸውና» (ይባላል)፡፡

  • 25. (ለእነርሱም) «የማትረዳዱት ለእናንተ ምን አላችሁ? (ይባላሉ)፡፡

  • 26. በእርግጥ እነርሱ ዛሬ እጃቸውን የሰጡ ወራዳዎች ናቸው፡፡

  • 27. የሚወቃቀሱም ሆነው ከፊላቸው በከፊሉ ላይ ይመጣሉ፡፡

  • 28. (ለአስከታዮቹ) እናንተ ከስተቀኝ ትመጡብን ነበር ይላሉ፡፡

  • 29. (አስከታዮቹም) ይላሉ «አይደለም ፈጽሞ ምእምናን አልነበራችሁም፡፡

  • 30. «ለእኛም በእናንተ ላይ ምንም ስልጣን አልነበረንም፡፡ በእርግጥ እናንተ ጠማሞች ሕዝቦች ነበራችሁ፡፡

  • 31. «በእኛም ላይ የጌታችን ቃል ተረጋገጠብን፤ እኛ (ሁላችንም ቅጣቱን) ቀማሾች ነን፡፡

  • 32. «ወደ ጥምመት ጠራናችሁም፡፡ እኛ ጠማሞች ነበርንና» (ይላሉ)፡፡

  • 33. ስለዚህ እነርሱ በዚያ ቀን በቅጣቱ ነጋሪዎች ናቸው፡፡

  • 34. እኛ በአመጸኞች ሁሉ እንደዚሁ እንሠራለን፡፡

  • 35. እነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም በተባሉ ጊዜ ይኮሩ ነበሩ፡፡

  • 36. እኛ ለዕብድ ባለቅኔ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተው ነን? ይሉም ነበር፡፡

  • 37. አይደለም እውነቱን (ሃይማኖት) አመጣ፡፡ መልክተኞቹንም እውነተኛነታቸውን አረጋገጠ፡፡

  • 38. እናንተ አሳማሚውን ቅጣት በእርግጥ ቀማሾች ናችሁ፡፡

  • 39. ትሠሩትም የነበራችሁትን እንጂ ሌላን አትመነዱም፡፡

  • 40. ግን ምርጥ የሆኑት የአላህ ባሮች (ቅጣትን አይቀምሱም)፡፡

  • 41. እነዚያ ለእነርሱ የታወቀ ሲሳይ አላቸው፡፡

  • 42. ፍራፍሬዎች (አሏቸው) እነርሱም የተከበሩ ናቸው፤

  • 43. በድሎት ገነቶች ውስጥ፡፡

  • 44. ፊት ለፊት የሚታያዩ ሲሆኑ በአልጋዎች ላይ (ይንፈላሰሳሉ)፡፡

  • 45. ከሚመነጭ ወይን ጠጅ በያዘ ብርጭቆ በእነርሱ ላይ ይዞርባቸዋል፡፡

  • 46. ነጭ ለጠጪዎች ጣፋጭ ከኾነች፡፡

  • 47. በእርሷ ውስጥም ምታት የለባትም፡፡ እነርሱም ከእርሷ የሚሰክሩ አይደሉም፡፡

  • 48. እነርሱም ዘንድ ዓይናቸውን (በባሎቻቸው ላይ) አሳጣሪዎች የኾኑ ዓይናማዎች አልሉ፡፡

  • 49. እነርሱ ልክ የተሸፈነ (የሰጎን) ዕንቁላል ይመስላሉ፡፡

  • 50. የሚጠያየቁም ሆነው ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ይመጣሉ፡፡

  • 51. ከእነርሱ የሆነ ተናጋሪ ይላል «እኔ ጓደኛ ነበረኝ፡፡

  • 52. «በእርግጥ አንተ ከሚያምኑት ነህን? የሚል፡፡

  • 53. «በሞትንና ዐፈር አጥንቶችም በሆን ጊዜ እኛ በእርግጥ እንመረመራለን?» (የሚል)፡፡

  • 54. እናንተ ተመልካቾች ናችሁን? ይላል፡፡

  • 55. ይመለከታልም፤ በገሀነም መካከልም (ጓደኛውን) ያየዋል፡፡

  • 56. ይላል «በአላህ እምላለሁ፤ በእርግጥ ልታጠፋኝ ቀርበህ ነበር፡፡

  • 57. «የጌታየም ጸጋ ባልነበረ ኖሮ ወደ እሳት ከሚቀርቡት እሆን ነበር፡፡»

  • 58. (የገነት ሰዎች ይላሉ) «እኛ የምንሞት አይደለንምን?

  • 59. «የመጀመሪያይቱ መሞታችን ብቻ ስትቀር፡፡ እኛም የምንቅቀጣ አይደለንምን?» (ይላሉ)፡፡

  • 60. ይህ (ለገነት ሰዎች የተወሳው) እርሱ በእርግጥ ታላቅ ዕድል ነው፡፡

  • 61. ለዚህ ብጤ ሠሪዎች ይሥሩ፡፡

  • 62. በመስተንግዶነት ይህ ይበልጣልን? ወይስ የዘቁም ዛፍ?

  • 63. እኛ ለበዳዮች ፈተና አድርገናታል፡፡

  • 64. እርሷ በገሀነም አዘቅት ውስጥ የምትወጣ ዛፍ ናት፡፡

  • 65. እንቡጧ ልክ የሰይጣናት ራሶች ይመስላል፡፡

  • 66. እነርሱም ከእርሷ በይዎች ናቸው፤ ሆዶችንም ከእርሷ ሞይዎች ናቸው፡፡

  • 67. ከዚያም ለእነርሱ በእርሷ ላይ ከተኳሳ ውሃ ቅልቅል (መጠጥ) አልላቸው፡፡

  • 68. ከዚያም መመለሻቸው ወደ ተጋጋመች እሳት ነው፡፡

  • 69. እነሱ አባቶቻቸውን የተሳሳቱ ሆነው አግኝተዋልና፡፡

  • 70. እነሱም በፈለጎቻቸው ላይ ይገሰግሳሉና፡፡

  • 71. ከእነርሱ በፊትም የቀድሞዎቹ (ሕዝቦች) አብዛኞቻቸው በእርግጥ ተሳስተዋል፡፡

  • 72. በውስጣቸውም አስፈራሪዎችን በእርግጥ ልከናል፡፡

  • 73. የተስፈራሪዎቹም መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከት፡፡

  • 74. ምርጥ የሆኑት የአላህ ባሮች ብቻ ሲቀሩ፡፡

  • 75. ኑሕም በእርግጥ ጠራን፡፡ ጥሪውን ተቀባዮቹም ምንኛ አማርን!

  • 76. እርሱንም ቤተሰቦቹንም ከከባድ ጭንቅ አዳንን፡፡

  • 77. ዘሮቹንም እነርሱን ብቻ ቀሪዎች አደረግን፤

  • 78. በርሱም ላይ በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ (መልካም ዝናን) ተውን፡፡

  • 79. «በዓለማት ውስጥ ሰላም በኑሕ ላይ ይኹን፡፡»

  • 80. እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡

  • 81. እርሱ ከምእምናን ባሮቻችን ነውና፡፡

  • 82. ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን፡፡

  • 83. ኢብራሂምም በእርግጥ ከተከታዮቹ ነው፡፡

  • 84. ወደ ጌታው በቅን ልብ በመጣ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)፡፡፡

  • 85. «ለአባቱና ለሕዝቦቹ ምንን ትግገዛላችሁ?» ባለ ጊዜ፡፡

  • 86. «ለቅጥፈት ብላችሁ ከአላህ ሌላ አማልክትን ትሻላችሁን?

  • 87. «በዓለማትም ጌታ ሃሳባችሁ ምንድን ነው?» አለ፡፡

  • 88. በከዋክብትም መመልከትን ተመለከተ፡፡

  • 89. «እኔ በሽተኛ ነኝም» አለ፡፡

  • 90. ከእርሱም የሸሹ ሆነው ኼዱ፡፡

  • 91. ወደ አማልክቶቻቸውም ተዘነበለ፡፡ አለም፡- «አትበሉምን?»

  • 92. «የማትናገሩት ለናንተ ምን አላችሁ?»

  • 93. በኀይል የሚመታቸውም ሆኖ በእነርሱ ላይ በድብቅ ተዘነበለ፡፡

  • 94. ወደእርሱም (ሰዎቹ) እየሮጡ መጡ፡፡

  • 95. አላቸው «የምትጠርቡትን ትግገዛላችሁን?»

  • 96. «አላህ እናንተንም የምትሠሩትንም የፈጠረ ሲኾን፡፡»

  • 97. «ለእርሱም ግንብን ገንቡ በእሳት ነበልባል ውስጥ ጣሉትም» አሉ፡፡

  • 98. በእርሱም ተንኮልን አሰቡ፡፡ ዝቅተኞችም አደረግናቸው፡፡

  • 99. አለም «እኔ ወደ ጌታዬ ኼያጅ ነኝ፡፡ በእርግጥ ይመራኛልና፡፡»

  • 100. ጌታዬ ሆይ! ከመልካሞቹ የሆነን (ልጅ) ስጠኝ፡፡

  • 101. ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም አበሰርነው፡፡

  • 102. ከእርሱ ጋርም ለሥራ በደረሰ ጊዜ «ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ እኔ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ?» አለው፡፡ «አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ሥራ፡፡ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ» አለ፡፡

  • 103. ሁለቱም ትዕዛዙን በተቀበሉና በግንባሩም ጎን ላይ በጣለው ጊዜ (የሆነው ሆነ)፡፡

  • 104. ጠራነውም፤ (አልነው) «ኢብራሂም ሆይ!

  • 105. ራእይቱን በእውነት አረጋገጥክ፡፡» እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡

  • 106. ይህ እርሱ በእውነት ግልጽ ፈተና ነው፡፡

  • 107. በታላቅ ዕርድም (መስዋዕት) ተቤዠነው፡፡

  • 108. በእርሱም ላይ በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ መልካም ዝናን አስቀረንለት፡፡

  • 109. ሰላም በኢብራሂም ላይ ይሁን፡፡

  • 110. እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን ሁሉ እንመነዳለን፡፡

  • 111. እርሱ በእርግጥ ካመኑት ባሮቻችን ነው፡፡

  • 112. በኢስሐቅም አበሰርነው፡፡ ከመልካሞቹ የሆነ ነቢይ ሲሆን፡፡

  • 113. በእርሱና በኢስሐቅ ላይም ባረክን፡፡ ከሁለቱም ዘሮች በጎ ሠሪ አልለ፡፡ ለነፍሱ ግልጽ በዳይም አለ፡፡

  • 114. በሙሳና በሃሩን ላይም በእርግጥ ለገስን፡፡

  • 115. እነርሱንም ሕዝቦቻቸውንም ከታላቅ ጭንቅ አዳንን፡፡

  • 116. ረዳናቸውም፡፡ እነርሱም አሸናፊዎች ነበሩ፡፡

  • 117. በጣም የተብራራውንም መጽሐፍ ሰጠናቸው፡፡

  • 118. ቀጥተኛውንም መንገድ መራናቸው፡፡

  • 119. በሁለቱም ላይ በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ መልካም ዝናን ተውንላቸው፡፡

  • 120. ሰላም በሙሳና በሃሩን ላይ ይሁን፡፡

  • 121. እኛ እንደዚሁ በጎ አድራጊዎችን ሁሉ እንመነዳለን፡፡

  • 122. ሁለቱም በእርግጥ ከአመኑት ባሮቻችን ናቸው፡፡

  • 123. ኢልያስም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነው፡፡

  • 124. ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ አላህን አትፈሩምን?

  • 125. በዕልን ትገዛላችሁን? ከሰዓሊዎቹ ሁሉ ይበልጥ በጣም አሳማሪ የሆነውንም አምላክ ትተዋላችሁን?

  • 126. አላህን ጌታችሁንና የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁን ጌታ (ትተዋላችሁን)?

  • 127. አስተባበሉትም፡፡ ስለዚህ እነርሱ (ለቅጣት) የሚጣዱ ናቸው፡፡

  • 128. ንጹሕ የተደረጉት የአላህ ባሮች ብቻ ሲቀሩ፡፡

  • 129. በእርሱ ላይም በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ መልካም ዝናን ተውንለት፡፡

  • 130. ሰላም በኢልያሲን ላይ ይሁን፡፡

  • 131. እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡

  • 132. እርሱ በእርግጥ ከምእመናን ባሮቻችን ነው፡፡

  • 133. ሉጥም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነው፡፡

  • 134. እርሱንና ቤተሰቦቹን ሁሉንም በአዳንናቸው ጊዜ (አስታውስ)፡፡

  • 135. (በቅጣቱ ውስጥ) ከቀሪዎቹ የሆነችው አሮጊት ብቻ ስትቀር፡፡

  • 136. ከዚያም ሌሎቹን አጠፋን፡፡

  • 137. እናንተም ያነጋችሁ ስትሆኑ በእነርሱ (መኖሪያዎች) ላይ (በቀን) ታልፋላችሁ፡፡

  • 138. በሌሊትም (ታልፋላችሁ)፤ ልብም አታደርጉምን?

  • 139. ዩኑስም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነው፡፡

  • 140. ወደ ተመላው መርከብ በኮበለለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

  • 141. ዕጣም ተጣጣለ፡፡ ከተሸነፉትም ሆነ፡፡

  • 142. እርሱም ተወቃሽ ሲሆን ዐሳው ዋጠው፡፡

  • 143. እርሱ ለጌታው ከአወዳሾቹ ባልሆነም ኖሮ፤

  • 144. እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ በሆዱ ውስጥ በቆየ ነበር፡፡

  • 145. እርሱ በሽተኛ ሆኖ በቃይ በሌለው (በባሕር) ዳርቻ ላይ ጣልነውም፡፡

  • 146. በእርሱም ላይ (በአጠገቡ) ከቅል የሆነችን ዛፍ አበቀልን፡፡

  • 147. ወደ መቶ ሺሕ ሰዎችም (ዳግመኛ) ላክነው፡፡ ከቶውንም ይጨምራሉ፡፡

  • 148. አመኑም፡፡ እስከ ጊዜ ድረስም አጣቀምናቸው፡፡

  • 149. (የመካን ሰዎች) ጠይቃቸውም፡፡ «ለጌታህ ሴቶች ልጆች ለእነርሱም ወንዶች ልጆች ይኖራልን?»

  • 150. ወይስ እኛ እነርሱ የተጣዱ ሆነው መላእክትን ሴቶች አድርገን ፈጠርን?

  • 151. ንቁ! እነርሱ ከቅጥፈታቸው (የተነሳ) ይላሉ፡-

  • 152. «አላህ (መላእክትን) ወለደ፡፡» እነርሱም በእርግጥ ውሸታሞች ናቸው፡፡

  • 153. በወንዶች ልጆች ላይ ይልቅ ሴቶችን ልጆች መረጥን?

  • 154. ለእናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ!

  • 155. አትገነዘቡምን?

  • 156. ወይስ ለእናንተ ግልጽ አስረጅ አላችሁን?

  • 157. «እውነተኞች እንደ ሆናችሁ መጽሐፋችሁን አምጡ» (በላቸው)፡፡

  • 158. በአላህና በአጋንንት መካከልም ዝምድናን አደረጉ፡፡ አጋንንትም እነርሱ (ይህን ባዮች በእሳት) የሚጣዱ መሆናቸውን በእርግጥ ዐውቀዋል፡፡

  • 159. አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ፡፡

  • 160. ግን የተመረጡት የአላህ ባሮች (በአላህ ላይ አይዋሹም)፡፡

  • 161. እናንተም የምትገዟቸውም ሁሉ፤

  • 162. በእርሱ (በአላህ) ላይ አንድንም አጥማሚዎች አይደላችሁም፡፡

  • 163. ያንን እርሱ ገሀነምን ገቢ የሆነውን ሰው ቢሆን እንጅ፡፡

  • 164. (ጂብሪል አለ) ከእኛም አንድም የለም፤ ለእርሱ የታወቀ ደረጃ ያለው ቢሆን እንጅ፡፡

  • 165. እኛም (ጌታን ለመግገዛት) ተሰላፊዎቹ እኛ ነን፡፡

  • 166. እኛም (አላህን) አጥሪዎቹ እኛ ነን፡፡

  • 167. እነርሱም (ከሓዲዎቹ) በእርግጥ ይሉ ነበሩ፡-

  • 168. «ከቀድሞዎቹ (መጻሕፍት) ገሳጭ መጽሐፍ እኛ ዘንድ በነበረን ኖሮ፤

  • 169. «የአላህ ምርጦች ባሮች በሆን ነበር፡፡»

  • 170. ግን (ቁርኣኑ በመጣላቸው ጊዜ) በእርሱ ካዱ፡፡ ወደፊትም በእርግጥ ያውቃሉ፡፡

  • 171. (የእርዳታ) ቃላችንም መልክተኞች ለሆኑት ባሮቻችን በእውነት አልፋለች፡፡

  • 172. እነርሱ ተረጂዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡

  • 173. ሰራዊቶቻችንም በእርግጥ አሸናፊዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡

  • 174. ከእነርሱም (ከመካ ከሓዲዎች) እስከ ጥቂት ጊዜ ድረስ ዙር (ተዋቸው)፡፡

  • 175. እያቸውም ወደፊትም (የሚደርስባቸውን) ያያሉ፡፡

  • 176. በቅጣታችንም ያቻኩላሉን?

  • 177. በቀያቸውም በወረደ ጊዜ የተስፈራሪዎቹ ንጋት ከፋ!

  • 178. እነርሱንም እስከ (ጥቂት) ጊዜ ድረስ ተዋቸው፡፡

  • 179. ተመልከትም በእርግጥም ያያሉ፡፡

  • 180. የማሸነፍ ጌታ የሆነው ጌታህ ከሚሉት ሁሉ ጠራ፡፡

  • 181. በመልክተኞቹም ላይ ሰላም ይኹኑ፤

  • 182. ምስጋናም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይሁን፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo