• 1. በኃይል አውጪዎች በኾኑት፤

  • 2. በቀስታ መምዘዝንም መዘዦች በኾኑት፤

  • 3. መዋኘትም ዋኚዎች በኾኑት፤

  • 4. መቅደምንም ቀዳሚዎች በኾኑት፤

  • 5. ነገርንም አስተናባሪዎች በኾኑት (መላእክት) እምላለሁ፡፡ (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡

  • 6. ተርገፍጋፊይቱ (ምድር) በምትርገፈገፍበት ቀን፤

  • 7. ለጣቂይቱ የምትከተላት ስትኾን (ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡

  • 8. በዚያ ቀን ልቦች ተሸባሪዎች ናቸው፡፡

  • 9. ዓይኖቻቸው ተዋራጆች (አቀርቃሪዎች) ናቸው፡፡

  • 10. «እኛ ወደ መጀመሪያይቱ ኹነታ ተመላሾች ነን?» ይላሉ፡፡

  • 11. «የበሰበሱ አጥንቶች በኾን ጊዜ (እንቀሰቀሳለን?)»

  • 12. «ይህቺ ያን ጊዜ ባለ ከሳራ መመለስ ናት» ይላሉ፡፡

  • 13. እርሷም አንዲት ጩኸት ብቻ ናት፡፡

  • 14. ወዲያውኑም እነርሱ እንቅልፍ በሌለባት (ምድር) ላይ ይኾናሉ፡፡

  • 15. የሙሳ ወሬ መጣልህን?

  • 16. ጌታው በተቀደሰው ሸለቆ በጡዋ በጠራው ጊዜ፤

  • 17. ወደ ፈርዖን ኺድ፡፡ እርሱ ወሰን አልፏልና፡፡

  • 18. በለውም፡- «ወደ መጥራራትህ ላንተ (መንገድ) አለህን?»

  • 19. «ወደ ጌታህም ልመራህ ትፈራውም ዘንድ፤ (መንገድ አለህን?)» አለው፡፡

  • 20. ታላቂቱንም ተዓምር አሳየው፡፡

  • 21. አስተባበለም፤ አመጸም፡፡

  • 22. ከዚያም (ለማጥፋት) የሚተጋ ኾኖ ዞረ፡፡

  • 23. (ሰራዊቶቹን) ሰበሰበም፤ ተጣራም፡፡

  • 24. አለም፡- «እኔ ታላቁ ጌታችሁ ነኝ፡፡»

  • 25. አላህም በኋለኛይቱና በፊተኛይቱ (ቃል) ቅጣት ያዘው፡፡

  • 26. በዚህ ውስጥ ለሚፈራ ሰው በእርግጥ መገምገሚያ አለበት፡፡

  • 27. ባፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይንስ ሰማይ? (አላህ) ገነባት፡፡

  • 28. ከፍታዋን አጓነ፤ አስተካከላትም፡፡

  • 29. ሌሊቷንም አጨለመ፡፡ ቀንዋንም ገለጸ፡፡

  • 30. ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት፡፡

  • 31. ውሃዋንና ግጦሿን ከእርሷ አወጣ፡፡

  • 32. ጋራዎችንም አደላደላቸው፡፡

  • 33. ለእናንተና ለእንስሶቻችሁ መጣቀሚያ ይኾን ዘንድ (ይህን አደረገ)፡፡

  • 34. ታላቂቱም መዐት በመጣች ጊዜ፣

  • 35. ሰው ሁሉ የሠራውን በሚያስታውስበት ቀን፣

  • 36. ገሀነምም ለሚያይ ሰው በተገለጠች ጊዜ፣

  • 37. የካደ ሰውማ፣

  • 38. ቅርቢቱንም ሕይወት የመረጠ፣

  • 39. ገሀነም እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት፡፡

  • 40. በጌታው ፊት መቆምን የፈራ ሰውማ ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለ

  • 41. ገነት እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት፡፡

  • 42. «ከሰዓቲቱ መቼ ነው መኾኛዋ?» ሲሉ ይጠይቁሃል፡፡

  • 43. አንተ እርሷን ከማስታወስ በምን ውስጥ ነህ?

  • 44. (የዕውቀት) መጨረሻዋ ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡

  • 45. አንተ የሚፈራትን ሰው አስፈራሪ ብቻ ነህ፡፡

  • 46. እነርሱ በሚያዩዋት ቀን ያንዲት ቀን ምሽትን ወይም ረፏዷን እንጅ ያልቆዩ ይመስላሉ፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo