1. ሐ.መ (ሓ ሚም)፡፡
2. ገላጭ በኾነው መጽሐፍ እምላለሁ፡፡
3. እኛ ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን አደረግነው፡፡
4. እርሱም በመጽሐፎቹ እናት ውስጥ እኛ ዘንድ በእርግጥ ከፍተኛ ጥበብ የተመላ ነው፡፡
5. ድንበር አላፊዎች ሕዝቦች ለመኾናችሁ ቁርኣኑን ከእናንተ ማገድን እናግዳለን?
6. በፊተኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ከነቢይ ብዙን ልከናል፡፡
7. ከነቢይም አንድም የሚመጣላቸው አልነበረም በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩ ቢኾኑ እንጅ፡፡
8. ከእነርሱም በኀይል ይበልጥ የበረቱትን አጥፍተናል፡፡ የፊተኞቹም (አጠፋፍ) ምሳሌ አልፏል፡፡
9. «ሰማያትንና ምድርንም ማን ፈጠራቸው» ብለህ ብትጠይቃቸው «አሸናፊው ዐዋቂው (አላህ) በእርግጥ ፈጠራቸው» ይላሉ፡፡
10. (እርሱ) ያ ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ ያደረገላችሁ በርሷም ውስጥ ትምመሩ ዘንድ ለእናንተ መንገዶችን ያደረገላችሁ ነው፡፡
11. ያም ከሰማያ ውሃን በልክ ያወረደላችሁ ነው፡፡ በእርሱም የሞተችውን አገር ሕያው አደረግን፡፡ እንደዚሁ (ከመቃብራችሁ) ትውወጣላችሁ፡፡
12. ያም ዓይነቶችን ሁሉ የፈጠረ ለእናንተም ከመርከቦችና ከቤት እንስሳዎች የምትጋልቧቸውን ያደረገላችሁ ነው፡፡
13. በጀርባዎቹ ላይ እንድትደላደሉ ከዚያም በርሱ ላይ የተደላደላችሁ ጊዜ የጌታችሁን ጸጋ እንድታስታውሱ፤ እንድትሉም፡- «ያ ይህንን የማንችለው ስንኾን ለእኛ ያገራለን ጌታ ጥራት ይገባው፡፡
14. እኛም በእርግጥ ወደ ጌታችን ተመላሾች፤ነን» (እንድትሉ)፡፡
15. ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን (ልጅን) አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡
16. ከሚፈጥረው ውስጥ ሴቶች ልጆችን ያዘን? በወንዶች ልጆችም (እናንተን) መረጣችሁን?
17. አንዳቸውም ለአልረሕማን ምሳሌ ባደረገው ነገር (በሴት ልጅ) በተበሰረ ጊዜ እርሱ በቁጭት የተመላ ኾኖ ፊቱ የጠቆረ ይኾናል፡፡
18. በጌጥ (ተከልሶ) እንዲያድግ የሚደረገውን? እርሱም (ለደካማነቱ) በክርክር የሚያብራራውን ፍጡር (ሴትን) ለአላህ ያደርጋሉን?
19. መላእክትንም እነርሱ የአልረሕማን ባሮች የኾኑትን ሴቶች አደረጉ፡፡ ሲፈጠሩ ነበሩን? መመስከራቸው በእርግጥ ትጻፋለች፡፡ ይጠየቃሉም፡፡
20. «አልረሕማንም በሻ ኖሮ ባልተገዛናቸው ነበር» አሉ፡፡ ለእነርሱ በዚህ ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚዋሹ እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡
21. ከእርሱ (ከቁርኣን) በፊት መጽሐፍን ሰጠናቸውን? ስለዚህ እነርሱ እርሱን የጨበጡ ናቸውን?
22. ከቶውንም «እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት ላይ አገኘናቸው፡፡ እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተመሪዎች ነን» አሉ፡፡
23. (ነገሩ) እንደዚሁም ነው፡፡ ከበፊትህ በማንኛይቱም ከተማ ውስጥ አስፈራሪን አልላክንም፤ ቅምጥሎችዋ እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት ላይ አገኘን፤ እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተከታዮች ነን ያሉ ቢኾኑ እንጅ፡፡
24. (አስፈራሪው) «አባቶቻችሁን በእርሱ ላይ ከአገኛችሁበት ይበልጥ ቀጥተኛን (ሃይማኖት) ባመጣላችሁም?» አላቸው፡፡ «እኛ በእርሱ በተላካችሁበት ነገር ከሓዲዎች ነን» አሉ፡፡
25. ከእነርሱም ተበቀልን፡፡ ያስተባባዮቹም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከት፡፡
26. ኢብራሂምም ለአባቱና ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «እኔ ከምትግገዙት ሁሉ ንጹሕ ነኝ፡፡»
27. «ከዚያ ከፈጠረኝ በስተቀር (አልግገዛም)፡፡ እርሱ በእርግጥ ይመራኛልና፡፡»
28. በዝርዮቹም ውስጥ ይመለሱ ዘንድ (ባንድ አምላክ ማመንን) ቀሪ ቃል አደረጋት፡፡
29. ይልቅ እነዚህን (ቁረይሾችን)፣ አባቶቻቸውንም ቁርኣንና ገላጭ መልክተኛ እስከመጣላቸው ድረስ አጣቀምኳቸው፡፡
30. እውነቱም በመጣላቸው ጊዜ «ይህ ድግምት ነው፡፡ እኛም በእርሱ ከሓዲዎች ነን» አሉ፡፡
31. «ይህም ቁርኣን ከሁለቱ ከተሞች በታላቅ ሰው ላይ አይወረድም ኖሯልን?» አሉ፡፡
32. እነርሱ የጌታህን ችሮታ ያከፈፍላሉን? እኛ በቅርቢቱ ሕይወት ኑሯቸውን በመካከላቸው አከፋፍለናል፡፡ ከፊላቸውም ከፊሉን ሠራተኛ አድርጎ ይይዝ ዘንድ ከፊላቸውን ከከፊሉ በላይ በደረጃዎች (በሀብት) አበለጥን፡፡ የጌታህም ጸጋ (ገነት) ከሚሰበስቡት (ሃብት) በላጨ ናት፡፡
33. ሰዎችም (በክሕደት) አንድ ሕዝብ የሚኾኑ ባልነበሩ ኖሮ በአልረሕማን ፤ለሚክዱት ሰዎች (በዚህች ዓለም) ለቤቶቻቸው ከብር የኾኑን ጣራዎች በእነርሱ ላይ የሚወጡባቸውንም (የብር) መሰላሎች ባደረግንላቸው ነበር፡፡
34. ለቤቶቻቸውም ደጃፎችን በእነርሱ ላይ የሚደገፉባቸውንም አልጋዎች (ከብር ባደረግንላቸው ነበር)፡፡
35. የወርቅ ጌጥንም (ባደረግንላቸው ነበር)፡፡ ይህም ሁሉ የቅርቢቱ ሕይወት መጣቀሚያ እንጅ ሌላ አይደለም፤ (ጠፊ ነው)፡፡ መጨረሻይቱም አገር በጌታህ ዘንድ ለጥንቁቆቹ ናት፡፡
36. ከአልረሕማን ግሣጼ (ከቁርኣን) የሚደናበርም ሰው ለእርሱ ሰይጣንን እናስጠጋለን፡፡ ስለዚህ እርሱ ለእርሱ ቁራኛ ነው፡፡
37. እነርሱም (ተደናባሪዎቹ) ተመሪዎች መኾናቸውን የሚያስቡ ሲኾኑ እነርሱ (ሰይጣናት) ከቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ ያግዷቸዋል፡፡
38. (በትንሣኤ) ወደኛ በመጣም ጊዜ (ቁራኛዬ ሆይ!) «በእኔና ባንተ መካከል የምሥራቅና የምዕራብ ርቀት በኖረ ወይ ምኞቴ! ምን የከፋህ ቁራኛ ነህ» ይላል፡፡
39. ስለ በደላችሁም ዛሬ እናንተ በቅጣት ተጋሪዎች መኾናችሁ አይጠቅማችሁም፤ (ይባላሉ)፡፡
40. አንተ ደንቆሮዎችን ታሰማለህን? ወይስ ዕውሮችንና በግልጽ ጥመት ውስጥ የኾኑን ሰዎች ትመራለህን?
41. አንተንም (ቅጣታቸውን ስታይ) ብንወስድህ እኛ ከእነርሱ ተበቃዮች ነን፡፡
42. ወይም ያንን የቀጠርናቸውን ብናሳይህ እኛ በእነርሱ (ቅጣት) ላይ ቻይዎች ነን፡፡
43. ያንንም ወደ አንተ የተወረደልህን አጥብቀህ ያዝ፡፡ አንተ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ነህና፡፡
44. እርሱም (ቁርኣን) ለአንተ፣ ለሕዘቦችህም ታላቅ ክብር ነው፡፡ ወደ ፊትም (ከርሱ) ትጠየቃላችሁ፡፡
45. ከመልእክተኞቻችንም ካንተ በፊት የላክናቸውን (ተከታዮቻቸውን) ከአልረሕማን ሌላ የሚገዙዋቸው የኾኑን አማልክት አድርገን እንደ ኾነ ጠይቃቸው፡፡
46. ሙሳንም በተዓምራቶቻችን ወደ ፈርዖንና ወደ ሹማምንቶቹ በእርግጥ ላክን፡፡ «እኔ የዓለማት ጌታ መልክተኛ ነኝ» አላቸውም፡፡
47. በተዓምራታችንም በመጣባቸው ጊዜ ወዲያውኑ እነርሱ በእርሷ ይስቃሉ፡፡
48. ከተዓምርም አንዲትንም አናሳያቸውም እርሷ ከብጤዋ በጣም የበለጠች ብትኾን እንጅ፡፡ (ከክህደታቸው) ይመለሱም ዘንድ በቅጣት ያዝናቸው፡፡
49. «አንተ ድግምተኛ (ዐዋቂ) ሆይ! ጌታህን አንተ ዘንድ ቃል በገባልህ ለእኛ ለምንልን፡፡ እኛ (ቅጣቱን ቢያነሳልን) ተመሪዎች ነን» አሉም፡፡
50. ስቃዩን ከእነርሱ ላይ በገለጥንም ጊዜ ወዲያውኑ ኪዳናቸውን ያፈርሳሉ፡፡
51. ፈርዖንም በሕዝቦቹ ውስጥ ተጣራ፡፡ አለም፤ «ሕዝቦቼ ሆይ! የምስር ግዛት የኔ አይደለምን? እነዚህም ጅረቶች ከስሬ የሚፈሱ ሲኾኑ (የኔ አይደሉምን?) አትመለከቱምን?
52. «በውነቱ እኔ ከዚህ ያ እርሱ ወራዳ ንግግሩንም ሊገልጽ የማይቀርብ ከኾነው በላጭ ነኝ፡፡
53. «በእርሱም ላይ የወርቅ አንባሮች ለምን አልተጣሉበትም ወይም መላእክት ከእርሱ ጋር ተቆራኝተው ለምን አልመጡም» (አለ)፡፡
54. ሕዝቦቹንም አቄላቸው፡፡ ታዘዙትም፡፡ እነርሱ አመጸኞች ሕዝቦች ነበሩና፡፡
55. ባስቆጡንም ጊዜ ከእነርሱ በተበቀለን፡፡ ሁሉንም አሰጠምናቸውም፡፡
56. (በጥፋት) ቀዳሚዎችና ለኋለኞቹ (መቀጣጫ) ምሳሌም አደረግናቸው፡፡
57. የመርየም ልጅም ምሳሌ በተደረገ ጊዜ ሕዝቦችህ (ከሓዲዎቹ) ወዲያውኑ ከእርሱ ይስቃሉ፡፡
58. «አማልክቶቻችን ይበልጣሉን ወይስ እርሱ?» አሉም፡፡ ለክርክርም እንጅ ላንተ እርሱን ምሳሌ አላደረጉትም፡፡ በእውነት እነርሱ ክርክረ ብርቱ ሕዝቦች ናቸው፡፡
59. እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤለም ልጆች ተዓምር ያደረግነው የኾነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
60. ብንሻም ኖሮ በምድር ላይ ከእናነተ ምትክ መላእክትን ባደረግን ነበር፡፡
61. እርሱም (ዒሳ) ለሰዓቲቱ (ማወቂያ) በእርግጥ ምልክት ነው፡፡ «በእርሷም አትጠራጠሩ፡፡ ተከተሉኝም፤ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» (በላቸው)፡፡
62. ሰይጣንም አያግዳችሁ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡
63. ዒሳ በታምራቶች በመጣ ጊዜም አላቸው «በእርግጥ በጥበብ መጣኋችሁ፡፡ የዚያንም በርሱ የምትለያዩበትን ከፊሉን ለናንተ ላብራራላችሁ (መጣሁ)፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ ታዘዙኝም፡፡
64. «አላህ ጌታዬ ጌታችሁም ነውና ተገዙት፡፡ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡»
65. ከመካከላቸውም አሕዛቦቹ ተለያዩ፡፡ ለእነዚያም ለበደሉት ከአሳማሚ ቀን ቅጣት ወዮላቸው፡፡
66. ሰዓቲቱን እነርሱ የማያውቁ ኾነው በድንገት ልትመጣባቸው እንጅ ይጠባበቃሉን?
67. ወዳጆች በዚያ ቀን ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት ነው፡፡ አላህን ፈሪዎች ብቻ ሲቀሩ፡፡
68. (ለነርሱስ) «ባሮቼ ሆይ! ዛሬ ቀን በእናንተ ላይ ፍርሃት የለባችሁም እናንተም የምታዝኑ አይደላችሁም» (ይባላሉ)፡፡
69. እነዚያ በአንቀጾቻችን ያመኑና ፍጹም ታዛዦች የነበሩ (ባሮቼ ሆይ!)
70. «ገነትን ግቡ እናንተም ሚስቶቻችሁም ትደሰታላችሁ ትከበሩም አላችሁ» (ይባላሉ)፡፡
71. ከወርቅ የኾኑ ሰፋፊ ዝርግ ሳሕኖችና ኩባያዎች በእነርሱ ላይ ይዝዞራሉ፡፡ በእርሷም ውስጥ ነፍሶች የሚከጅሉት፣ ዓይኖችም የሚደሰቱበት ሁሉ አልለ፡፡ እናንተም በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ናችሁ፡፡
72. ይህችም ያቺ ትሠሩት በነበራችሁት ዋጋ የተሰጣችኋት ገነት ናት፡፡
73. ለእናንተ በውስጧ ብዙ ፍረፍሬዎች በእርግጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
74. አመጸኞች በገሀነም ስቃይ ውስጥ በእርግጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
75. ከእነርሱ (ቅጣቱ) አይቀለልላቸውም፡፡ እነርሱም በእርሱ ውስጥ ተሰፋ ቆራጮች ናቸው፡፡
76. አልበደልናቸውምም፤ ግን በዳዮቹ እነርሱው ነበሩ፡፡
77. «ማሊክ ሆይ! ጌታህ በኛ ላይ (በሞት) ይፍረድ፡፡» እያሉ ይጣራሉም፡፡ «እናንተ (በቅጣቱ ውስጥ) ዘላለም ነዋሪዎች ናችሁ» ይላቸዋል፡፡
78. እውነተኛውን መንገድ በእርግጥ አመጣንላችሁ፡፡ ግን አብዛኞቻችሁ እውነቱን ጠይዎች ናችሁ፡፡
79. ይልቁንም (በነቢዩ ላይ በማደም) ነገርን አጠነከሩን? እኛም (ተንኮላቸውን ወደእነርሱ በመመለስ) አጠንካሪዎች ነን፡፡
80. ወይም እኛ ምስጢራቸውንና ውይይታቸውን የማንሰማ መኾናችንን ያስባሉን? አይደለም፤ መልክተኞቻችንም እነርሱ ዘንድ ይጽፋሉ፡፡
81. «ለአልረሕማን ልጅ (የለውም እንጅ) ቢኖረው እኔ (ለልጁ) የተገዢዎቹ መጀመሪያ ነኝ» በላቸው፡፡
82. የሰማያትና የምድር ጌታ የዙፋኑ ጌታ ከሚሉት ነገር ሁሉ ጠራ፡፡
83. ተዋቸውም፡፡ ያንን ይስፈራሩበት የነበሩትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ (በስሕተታቸው ውስጥ) ይዋኙ ይጫዎቱም፡፡
84. እርሱም ያ በሰማይ ውስጥ ሊግገዙት የሚገባው በምድርም ውስጥ ሊግገዙት የሚገባው አምላክ ነው፡፡ እርሱም ብልሃተኛው ዐዋቂው ነው፡፡
85. ያም የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የእርሱ ብቻ የኾነው አምላክ ላቀ፡፡ የሰዓቲቱም (የመምጫዋ ዘመን) ዕውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ፡፡
86. እነዚያም ከአላህ ሌላ የሚግገዟቸው እነርሱ የሚያውቁ ኾነው በእውነት ከመሰከሩት በስተቀር ምልጃን አይችሉም፡፡
87. ማን እንደፈጠራቸውም ብትጠይቃቸው «በእርግጥ አላህ ነው» ይላሉ፡፡ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ይዞራሉ፡፡
88. (ነቢዩ) ጌታዬ ሆይ! እነዚህ የማያምኑ ሕዝቦች ናቸው፤ የማለቱም (ዕውቀት አላህ ዘንድ ነው)፡፡
89. እነርሱንም ተዋቸው፡፡ ነገሬ ሰላም ነው በልም፡፡ ወደፊትም (የሚመጣባቸውን) ያውቃሉ፡፡